በሦስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን በአውሮፓ ህብረት በሁለት ሚሊየን ዩሮ የሚደገፈው የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
በሦስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን በአውሮፓ ህብረት በሁለት ሚሊየን ዩሮ የሚደገፈው የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ፣በትግራይ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተግባራዊ የሚሆን በአውሮፓ ህብረት በሁለት ሚሊየን ዩሮ የሚደገፈው በግጭት አፈታትና ሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ አካሄዷል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሰላም ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ እንደሆነ ገልፀው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ የሰላም እጦቶችን ለመቅረፍ በንግግር የመፍታት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እየፈታ ይገኛል ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ነባር እሴቶቻችንን በማጠናከር የሰላም እጦት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ሰላምን ለመገንባት ለሚሰራው ስራ አመስግነው ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል በማለት ገልፀዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር ካርመን ቲል በበኩላቸው ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ማለት አይደለም ፤ሰላም ማለት ተስፋ የሞላበት ፍቅር ያለበት ህይወት መለማመድ ማለት ነው ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለውም በዚህ ፕሮጀክት የምናደርገው የሰላም ግንባታ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን በማለት ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ 35ሺ ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በማጠናከር ፣ወጣቶችን የሰላም ግንባታ ስራ ባህላቸው አድርገው እንዲሰሩ በማድረግ እና የተሻለ የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ ሰላምን መገንባት ላይ ፕሮጀክቱ ይሰራል ተብሏል፡፡