….. በጎነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባሕላችን ነው
….. በጎነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባሕላችን ነው
ሀገራችን ዘርፈ-ብዙ የሆነ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት፣ የመልክዓ ምድር ወዘተ ብዝኃነት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ትውልዱ ይህን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያውቅ፣ እንዲያሳውቅ፣ እንዲያከብር፣ እንዲጠብቅ እና ለመጪ ትውልድ እንዲያስተላለፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር በሀገር ግንባታ ሥራ ውስጥ በትልቁ ሊተገበር የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ትውልዱ ሀገራዊ እሴቱን በውል ተገንዝቦ በሀገር ግንባታ ሂደቱ ላይ ሚናውን እንዲለይ፤ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ምን ምን ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት የጠራ ግንዛቤ እንዲጨብጥ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር የሰላም ሚኒስቴር ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ እያደረገ ያለው የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ብዙ አዎንታዊ ውጤቶችን ማስመዝገቡ በተግባር ታይቷል፡፡ ባገባደድነው የዕቅድ ዘመን ‹‹በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው የክረምቱ ልዩ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሀገራዊ ንቅናቄ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ሲሆን በተለይም የከፍተኛ ትምህረት ተቋማት ተማሪዎች በስፋት ተሳታፊ የሆኑበት ነው፡፡የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሀገራዊ ንቅናቄው፡- ተሳታፊዎች የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በነጻ በማገልገል የህሊና እርካታ ያገኙበት፣ ለበጎነት ተግባር ከአካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ከኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው ጋር ማኅበራዊ ትስስርን ያጠናከሩበት እና ሞራላቸውን የገነቡበት መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በዕቅድ ውስጥ ተካተው ከሚፈፀሙ መደበኛ ሥራዎች ባሻገር ሕዝብንና ሀገር ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመሥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆኑ በማድረግ እና ወጪዎችን በማስቀረት ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱበትም ነው፡፡
ችግሮችን በድል ለመሻገር፤ ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት፤ ሀገራዊ የጋራ ግቦቻችንን ለማሳካት የዜጎች ኅብረት፣ መደጋገፍ፣ የአብሮነት መጠናከር እና በጋራ መቆም የኢትዮጵያዊነታችን ባሕል ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ነባር እሴት የሆነውን የመረዳዳት ባሕላችንን አዳብረን ለወገኖቻችን በጎ ሥራ መሥራት ገና ከጅምሩ ውጤት ያሳየ ተግባር ስለሆነ ሊጠናከር የሚገባ መልካም ጅምር ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ !