የሰላም ግንባታ እና የሰላም ትምህርት ግንኙነት
የሰላም ግንባታ እና የሰላም ትምህርት ግንኙነት
የሰላም ግንባታ እና የሰላም ትምህርት ከፍተኛ የሆነ ትስስር አላቸው። የሰላም ግንባታ አዳዲስ ግንኙነቶችን እና ትስስሮችን የመገንባት ወይም ሰላምን መልሶ የመገንባት እና ነባሮቹን የማዘመን ሂደት ነው፡፡
የሰላም ግንባታው ወይም የመልሶ ግንባታው ሂደት ፍትሕን እና ሰብአዊ መብቶችን ያካተተ ነው። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ጤናማ ግንኙነት ወደ ነበረበት በመመለስ ከዚህ በፊት ተጋጭተው የነበሩ ወገኖችን በማስታረቅ ወይም አስታራቂ ፍትሕን በመጠቀም ሰላማዊ ግንኙነት በግለሰቦችና በማህበረሰቡ ዉስጥ እንዲሰፍን ማስቻል ነው፡፡
የሰላም ግንባታ አስከፊ ግጭት ከመከሰቱ በፊት ወይም ግጭቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሊከናወን ይችላል። የሰላም ግንባታው ሂደት ሥር የሰደዱ ወይም መዋቅራዊ የግጭት ምክንያቶችን መፍትሔ በመስጠት ሰላማዊ አብሮነትን ያበረታታል። በአጭሩ የሰላም ግንባታ ሂደት በአካባቢና በብሔራዊ ደረጃ ሰላማዊ እና የተረጋጉ ማኅበረሰቦችን ከመገንባት አንጻር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
የሰላም ሚኒሰቴር የሰላም ግንባታ ስራዎችን ለማጠናከርና አወንታዊ ሰላም ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ለማሳደግ፤ግለሰብ፣ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሰላም ግንባታ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆን እና በሰላም አስተሳሰብ ላይ የጋራ ግናዛቤ ለመያዝ የሰላም ትምህርት መስጠት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡