የሰላምና ልማት ነባር የጋራ ግንኙነት የምክክርና የስልጠና መድረክ ተካሄደ
アセットパブリッシャー
የሰላም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ እና ከአማራ ክልሎች ከመጡ ተሳታፊዎች እና ከሰላም ሚኒስቴር የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር “የሰላምና ልማት ነባር የጋራ ግንኙነት የምክክርና የስልጠና መድረክ” አካሂዷል።

በስልጠናውን የሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝም እና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩ ጌታ ገነነ ተገኝተው በንግግር የከፈቱ ሲሆን፤ የመድረኩ ዓላማ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢ ያሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን በመለየትና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የጋራ ግንኙነት ማጠናከር እና በሴክተሩ የሚሰሩ አመራሮችንና ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የሰላም ሚኒስቴር የግጭት መከላከል እና አፈታት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋለም መንግስቱ “በሰላም ግንባታና ግጭት መከላከል” ሰነድ ያቀረቡት ሲሆን የግጭት ባለድርሻ አካላት ትንተና፣ የትንተና መሳሪያዎች፣ ግጭትን ማስተዳደርና አፈታት ፅንሰ ሀሳብ፣ የሰላም ባህል ስለመገንባት እና ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት የምንጠቀምባቸው ስልቶችንና ልንከተለው የሚገባ አሰራር በሚሉ ሀሳቦች ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡

“ፌዴራላዊ ፖለቲካዊ ባህል” በሚል ርዕስ ሁለተናውን ሰነድ ያቀረቡት ደግሞ የመንግስታት ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ግርማ ቸሩ ሲሆኑ በፖለቲካ ባህል እድገት እና ባህርያት ላይ ተፀዕኖ የሚያሳድሩ ቁልፍ ነገሮችን በመተንተን፤ በኢትዮጵያ ጤናማ የፌዴራል ፖለቲካ ባህል ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ሥርዓት ለመገንባት መሰረታዊ መሆኑን በመጥቀስ አብራርተዋል።
ሦስተኛውን ሰነድ በአቶ ፀጋብርሀን ታደሰ የቀረበ ሲሆን “ፌዴራሊዝም እና የመንግስታት ግንኙነት ምንነት” ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ የሰጡ ሲሆን፣ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ መሰረቶችንም አብራርተዋል።
በቀረቡት ሰነዶች ላይ ጥያቄና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በማጠቃለያ ላይም ግጭት በባህሪው ተፈጥሯዊ በመሆኑ ሁልጊዜም ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። አንዳንድ ግጭቶች በራሳቸው አቅም ሊፈቱ የሚችሉ፣ አንዳንዶች ፈጣን ምላሽ የሚያሻቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ የብዙ አካላትን ውይይት የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይቀየር የግጭቶችን አይነትና ባህርያት በማጥናት ማስቀረት እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን፤ችግሮች በሚከሰቱ ጊዜ ወረዳ፣ ዞን እና ፎረሞች በአንድላይ በመነጋገር መለየት ያስፈልጋል ተብሏል።
የግጭት አፈታት ስራዎች ተቋማዊ መሆን እንዳለባቸው እና የፖለቲካ ባህል ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ተቋማት ላይ ማለትም፡- የባህል፣ የሀይማኖት እና የፖለቲካ ልሂቃን የሚወያዩበት ፕላትፎርም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገልጾ፤ በሥራው ላይ ማህበረሰቡን ማሳተፍ ደግሞ መፍትሄውን እዛው ለማግኘት አንድ መንገድ በመሆኑ ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጿል።
ከዞንና አዋሳኝ ወረዳዎች፣ ከጋራ ሰላምና ልማት ቢሮ እና ከበይነ መንግስታት ቢሮዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች በስልጠናው ላይ ተገኝተዋል፡፡