ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላም
ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላም
ሀገራችንን እንደ ሀገር አጽንተው ካቆዩት የዜጎች አብሮ የመኖር መሰረቶች መካከል አወንታዊ ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶችና ሀብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግስታዊ ተግባራትንም በማገዝ ሰላማዊ ዜጋ እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
በወንድማማችነትና በአብሮነት ለዘመናት አብረው የኖሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቻቸውን አክብረው ዛሬም በፍቅርና በወንድማማችነት አብረው ይኖራሉ። ስለሆነም ያሉንን ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶቻችንን አጠናክሮ ማስቀጠል ሰላማዊ የሆነ ማህበራዊ መስተጋብርና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትን እንደሚፈጥር ዕሙን ነው።
መንግስት የሀገራችንን ሰላም ለማስፈን የራሱ የማይተካ ድርሻ ቢኖረውም ይህ ጉዳይ ለሱ ብቻ የሚተው ስራ አይደለም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ ዜጋ እና ማህበረሰብን ይመለከታል፡፡ በአፋር እንደ ዳጉ ያሉ ባህላዊ መረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት፤ እንደ ጋሞ አባቶች፤ እንደ ገዳ ስርዓት፣ ወዘተ… ያሉ ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን ሰላምን ለማስፈን አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡ እነዚህን በየአካባቢው ያሉ እና በትውልድ ቅብብሎሽ ያልደበዘዙ ማህበራዊ እሴቶቻችንን በማጠናከር ለሰላም ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል፡፡
እንደ ዜጋና ማህበረሰብ በየአካባቢያችን የሚከናወኑ ድርጊቶችን በንቃት በመከታተል እና ነባር ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ መከላከል ይኖርብናል፡፡እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀውን በአብሮነትና በወንድማማችነት ተከባብሮ የመኖር ማኅበረ-ባህላዊ እሴታችንን በማጽናት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!