በአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት 13ኛ ዙር የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተጀመረ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት 13ኛ ዙር የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና መክፈቻ መርሐ-ግብር በአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ ተከናውኗል፡፡

በመክፈቻ መርሐ-ግብሩን የከፈቱት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ሀገራዊ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆዎችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በብሔር ብሔረሰብ፣ በሀይማኖት፣ እና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለው ልዩነት ጌጥ እንጂ ዕዳ አለመሆኑን በመገንዘብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት በተለይም የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሮግራሙ የወጣቶችን የበጎ ፈቃድ ትስስርን ከማጠናከርና ለሀገር ግንባታ አስተዋፅኦ ከማበርካት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን እያቃለለ መሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ካመጣቸው ተጨባጭ ውጤቶች የሚጠቀስ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር አቶ ካይዳኪ በጎ ፈቃደኞች ለሰላም እሴት ግንባታ መጠናከር ያደረጉት አስተዋፅኦ ለአብነት የሚጠቀስና በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል “ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ የማይተካ ሚና እንዳላችሁ ተገንዝባችሁ ምንጫቸው በማይታወቅ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከሚተላለፉ ዜጎችን ከሚያራርቁ አፈራሽ ዘገባዎች እራሳችሁን እንድታርቁና ዜጎችን የሚያቀራርቡ፤ ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱ ይዘቶችን በማሰራጨት ኃላፊነታችሁን መወጣት ይኖርባቸዋል”፤ በማለት ለሰልጣኞች መልእክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ለሀገራዊ “ሰላማችን መረጋገጥ ሁላችሁም ፍትሐዊነትን በማስፈን የምታምኑ፤ የሀገረ-መንግሥት ግንባታን የምታጠናክሩ፤ የግብረገብነትና የሰላም እሴቶችን የምትሰብኩ፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ፍቅር ያላችሁ፣ ብዙኃነትን የምትቀበሉ፣ ሰብአዊ መብቶችን የምታከብሩ፣ በምክንያታዊ ትንተና እና በውይይት የምታምኑ እንድትሆኑ አደራ”፤ ሲሉም አክለዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገመቺሳ ኢትቻ ስለ ስልጠናው በሰጡት ማብራሪያ ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው በመልካም ሥነ ምግባርና ግብረ ገብ የዩኒቨርሲውን ደንቦች በመጠበቅ እንዲንቀሳቀሱ እና ለሌሎች መልካም አርአያ እንዲሆኑ በማሳሰብ ሰልጣኞች ኢትዮጵያዊ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን እና እሴቶቻችን በመጋራት ሀገራዊ ሕብር የሚያጠናክሩበት፤ በስልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገርን እና ወገንን ለማገልገል የሚዘጋጁበት መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ የሰላም አምባሳደር እና የበጎነት ተምሳሌት የመሆን ኃላፊነታቸውን በጥብቅ ድስፕሊን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።