ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፣ በ13 ኛው ዙር መርሐ-ግብር ስልጠናቸውን ለመከታተል በአርባምንጭ፣ ጅግጅጋ፣ ወሎ፣ መቱ እና አሶሳ ዩኒቨርስቲዎች የገቡ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ተሳታፊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሄደ።
የሰላም ሚኒስቴር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ በሥነ ምግባር፣ በክሕሎት እና በሥራ ፈጠራ ግንዛቤ የሚያዳብር ስልጠና በመስጠት እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በማሰማራት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ፕሮግራሙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቀሰሙትን ዕውቀት እና የተለያዩ ሙያ ከተሰጣቸው ስልጠና ጋር በማስተሳሰር በበጎ ፈቃደኝነት ለማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት በዜጎች መካከል ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎልብት፣ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር በማድረግ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበት ነው፡፡
"በጎነት ለአብሮነት"
በሚል መሪ ሃሳብ በሰላም ሚኒስቴር የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ በማድረግ ፤ በማንነቶች ላይ መሰረት አድርጎ ያለውን መጠነኛ መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ማረጋገጥ ነው።
የሰላም ሚኒስቴር በ12 ዙር ባካሄደው ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ከ80 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አገልግሎታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ለ13ኛ ዙር በሚሰጠው ስልጠና በአምስቱም ዩኒቨርስቲዎች 5ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተደርጎላቸዋል።