ለዘላቂ ሰላም እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን - የሶማሌና አፋር ክልል የህብረተሰብ ክፍሎች
ለዘላቂ ሰላም እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን - የሶማሌና አፋር ክልል የህብረተሰብ ክፍሎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17 ቀን 2017(ኢዜአ)፡- በሶማሌ እና አፋር ክልሎች ዘላቂ ሰላምን እና የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የክልሎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በውይይቱ ከሶማሌ ክልል የተሳተፉት በሺር አሕመድ፥ በውይይቱ የተደረሱ ስምምነቶችን ወደ ህብረተሰቡ ለማውረድ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በክልሎቹ መካከል የተገኘውን ሰላም ለመጠበቅና ለማጽናት ሁሉም የራሱን ድርሻ በመውሰድ እንዲሰራም ነው የጠየቁት።
ከአፋር ክልል የተሳተፉት አይሻ ያሲን፥ መድረኩ አስተማሪ እና ትልቅ ልምድ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለመጪው ትውልድ ሰላምን ማውረስ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አንስተዋል።
የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑና ይህንንም ለማድረግ በመድረኩ ቃል መግባታቸውን የተናገሩት ደግሞ ከአፋር ክልል የመጡት አስተያየት ሰጭ መሀመድ ደረስ ናቸው።
ከአፋር በመድረኩ የተሳተፉት አሊ ሳልህ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ህዝቦች ብዙ የጋራ ታሪክ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠልም የጋራ ተስፋዎችን ማየት እንደሚገባ ነው ያነሱት።
ከሶማሌ ክልል የተሳተፉት ሂስ አህመድም በቀጣይ ወደ ማህበረሰቡ በመውረድ ሰላምን ለማጽናትና አብሮነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ሌላኛው የሶማሌ ክልል ተሳታፊ ኑር ሀሰን ሰላምና አንድነት የልማት መሰረት መሆኑን ጠቁመው የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሰላም ዘብ መቆም፣ አብሮነት እና አንድነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፥ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ ማህበረሰቡን በተለያየ መንገድ ስለሰላም የማስተማር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁንም የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ፥ በመድረኩ በክልሎቹ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።
መድረኩ አለመግባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን በመጠቆም።
በዛሬው ዕለት የተመሰረተው የሶማሌ እና የአፋር ክልል ህዝቦች የሰላም እና ልማት ፎረምም ሁለቱ ህዝቦች ለጋራ ሰላም እና አንድነት የሚሰሩበት ነው ብለዋል።
ፎረሙ በጋራ እሴቶቻቸው ዙሪያ የሚመክሩበት መሆኑንም ገልጸዋል።