ኢትዮጵያዊ በጎ እሴቶች ለማኅበረሰባዊ ግንኙነትና ሰላም
ኢትዮጵያዊ በጎ እሴቶች ለማኅበረሰባዊ ግንኙነትና ሰላም
እሴቶቻችን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ልዩ ልዩ መልክና ሥርዓት ያላቸው ሆነው ለብዝኃነታችን ልዩ ውበት የሚሰጡ፣ የዜጎችን ክብርና ደህንነት የሚያስጠብቁ፣ ማኅበረሰቦች ለሰላም በጋራ እንዲቆሙ፣ ለአካባቢ ልማት በሕብረት እንዲሠሩ፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
በአሁን ጊዜ በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት የሚታዩ የሰላም ችግሮች መነሻቸው ከፖለቲካ ፍላጎት በተጨማሪ እሴቶቻችን መሸርሸር ያመጣቸው ችግሮች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ እነዚህ መልካም እሴቶች ሀገር የምታራምደውን ሁለንተናዊ የሰላም፣ የአብሮነትና የአንድነት ጉዞ እንዲሁም የልማትና ዕድገት ስትራቴጂዎችን የሚደግፉ ስለሆኑ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ በጎ እሴቶች እንዳይደበዝዙ ተጠብቀው መያዝና ለትውልድ መተላለፍ ያለባቸው ናቸው፡፡
መልካም እሴቶች እንዳይሸረሸሩ መጠበቅ፣ መንከባከብና ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተነሳሽነት፣ ጥረትና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡
ከሌሎች ሀገሮችና ሕዝቦች ልምድ ወስደን ብንተገብራቸው የምንጠቀምባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የሀገራችንን መልካም እሴቶች እየሸረሸሩ የሌሎችን ጎጂ ልማዶች የሚያስፋፉ የዓለም አቀፋዊነት (Globalization) አሉታዊ ተፅእኖዎችን መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ የራሳችንን መልካም እሴቶች በማጎልበት በግልም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚገጥሙንን ችግሮች ተነጋግሮ መፍታት እና የሰላም እንቅፋት እየሆኑ የሚታዩ ችግሮችን መሻገር ያስፈልጋል፡፡
ሰላም ለኢተዮጵያ !