ኢትዮጵያና ሞሮኮ በሰላም ግንባታ ላይ አብሮ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
Tartalom megjelenítő
ሰኔ 4/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ከሆኑት ክብርት ወ/ሮ ነዛሃ አላኦኢ ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገር መሆናቸውን ገልፀው ሁለቱ ሀገሮች በባህል፣ በሐይማኖት እና በሌሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም ሚኒስቴር እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት በተለይም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት እና መሰረታዊ የሀገር መንግስት ግንባታ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል፡፡
የዛሬው ውይይት ኢትዮጵያና ሞሮኮ በቀጣይ በሰላም ግንባታ እና በአብሮነት ላይ ለሚያከናውኑት ተግባራት አመች ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የሞሮኮ አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ ነዛሃ አላኦኢ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያጋጠማት ያለውን ችግር የምታልፍበት መንገድ እና ፈተናን የመቋቋም አቅምን እንደሚያደንቁ ገልፀው ሞሮኮ ከዚህ ትልቅ ትምህርት ትወሳዳለች ብለዋል፡፡
በቀጣይ የኢትዮጵያና ሞሮኮ በሰላም ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ አብረው እንደሚሰሩ የገለፁት አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ ነዛሃ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል የሞሮኮ ንጉስ መሀመድ አምስተኛ ፋውንዴሽን በአዲስ አዲስ አበባ እንደሚከፍቱ እና የሰላም ሚኒስቴር አመራሮችን እና የሐይማኖት መሪዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ሞሮኮን እንዲጎበኝ ግብዣ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “የኢትዮጵያ ሞሮኮ የጋራ ኮሚሽን” ለመመስረት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ ነዛሃ አላኦኢ ተናግረዋል፡፡