የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ምንድን ነው?
የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ምንድን ነው?
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣን እና ተግባራት መካከል ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ የባህል ልውውጥ ስራዎችን እንደሚያከናውንና በህብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና የንቅናቄ ስልቶችን በመቀየስ እንደሚሰራ ተቀምጧል።
ተቋማችን ከላይ በአዋጅ የተሰጡት ተግባራት ለማካናወን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ “በጎነት ለአብሮነት” በሚል ፅንስ ሃሳብ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በመንደፍ በርካታ ወጣቶችን እያሳተፈ ይገኛል፡፡
ይህ ፕሮግራም በታሪክ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩ እና የተዛነፉ ትርክቶችን ለማስተካከል ወጣቶችን ከሚኖሩበት አካባቢ ወጥተው ወደ ማያውቁት አካባቢ/ክልል/ በመሄድ የማያውቁትን ማህበረሰብ እንዲመለከቱ፣ሌላኛውን የኢትዮጵያ ጫፍ በእግራቸው ረግጠው በአቅማቸው አገልግለው የሀገር ፍቅርን እንዲያዳብሩ እና በሂደቱ ደግሞ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ወንድማማችነትን እንዲጠናክሩ የተቀየሰ እና እየተሰራበት ያለ ፕሮግራም ነው፡፡
የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ ኢትዮጵያ ያሏትን መልካም እሴቶች፣መርሆዎች፣ የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ የወጣቶችን ምክንያታዊነትን፣ የሕይወት መምራት ክሕሎትን፣ የሥራ ባሕልን፣ መልካም ሥነ ምግባርን በማጎልበት፤ አገራዊ አንድነትን እና ብሔራዊ መግባባትን በማስረጽ ዘላቂ ሰላም መገንባት ነው ፡፡
በጎ ፈቃደኝነት እና በነፃ ፍላጎት ህዝብንና ሀገርን ለማገልገል የዕውቀት፣የጉልበት እና የገንዘብ አበርክቶ ማድረግ ሲሆን የበጎ ፈቀድ አገልግሎት ዋጋ የህዝብ እርካታ እና መንፈሳዊ ሀሴት ማግኘት ነው፡፡ሀገር የተገነባቸው በበጎ ፈቃደኞች መልካም ፈቃድ እና ይሁንታ ሲሆን ዜጎች በሚችሉት አቅም ለሀገራቸው ሰላም እና ልማት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸውል፡፡የሀገር አንድነት እና ሰላም ሲረጋገጥ የሁሉም ተጠቃሚነት በዚያው ልክ ስለሚረጋገጥ በዚህ ሂደት የምናስቀምጠው አሻራ መልሶ ለራሳችን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
በጎነት ከሌለ የሚሰምር የሀገር ግንባታ የሚረጋገጥ የሀገር ሰላም ሊኖር አይችልም ፡፡ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ለአንድነት እና ለሰላም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስንሰጥ ሌሎችን ከማገዝ ባሻር ለራስ የሚሰጠው ጥቅምም ከፍተኛ ነው፡፡ይህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስንሰጥ አቅማችን፣ግንዛቤያችን ይዳብራል፤ ዕይታችን ይሰፋል፤የማናውቀውን እናውቃለን ፣የማንችለውን እንችላለን፣ ከምንም በላይ ደግሞ ሌሎችን በማገልገልችን የምናገኘው መንፈሳዊ ዕርካታ፣ የአይምሮ እረፍት ከፍ ያለ ነው፡፡
ብሔራዊ ስሜትና ኩራት እንዲሁም የኢትዮጵያ አንድነትን የተረዱ፣ በራስ መተማማናቸው ያደገ፣ ብቁ ፣ ተወዳዳሪ እና ማህበረሰብ ተኮር ባህሪን ያዳበሩና በሀገር ግንባታ ውስጥ ገንቢ በሆነ መንገድ ለመሳተፍ ዝግጁ የሆኑ ውጤቶች መፈጠር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ካስገኛቸው ዋና ዋና ውጤቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ !