በጎነት ለአብሮነት
በጎነት ለአብሮነት
የሰላም ሚኒስቴር ሀገራችን ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት እና ሀገራዊ መግባባት የጎለበተባት ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ተቋሙ ህዝቡን በማሳተፍና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የተለያዩ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሀገር ግንባታ ስራዎችን ለመስራት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡
ተቋማችን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ “በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በመንደፍ ለ11 ተከታታይ ዙር ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን እና በማሰማራት ከ75ሺህ በላይ ወጣቶችን ማሳተፍ ችሏል፡፡ የፕሮግራሙ ዓላማም ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን እና መርሆቻችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በጎሳ፣ በኃይማኖት መካከል ያለውን መከፋፈል እና ልዩነት በማስወገድ የወጣቶችን የሀገር እና የህዝብ ፍቅርን፣ ምክንያታዊነትን፣ የሕይወት መምራት ክህሎትን፣ የሥራ ባህልን፣ ሥነ-ምግባር በማጎልበት ሀገራዊ አንድነትን፣ ማኅበራዊ ትስስርን በማስፈን ብሔራዊ መግባባትን ማጎልበት እና ዘላቂ ሰላማችንን ዕውን ማድረግ ነው፡፡
ይህ ፕሮግራም በወጣቶች ስብዕና፣ አመለካከት እና የስራ ባህል ግንባታ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሚሳተፉ ወጣቶች ከተሳትፎ በኋላ በተሻለ ስብዕና፣ ሀገራዊ እውቀት እና የስራ ዝግጁነት ለሌሎች እኩዮቻቸው እና ታዳጊዎች ዓርአያ ሆነው ይወጣሉ ፡፡
እስካሁን በተሰሩ ስራዎች እና እየታዩ ባሉ ውጤቶች ይህ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ሀገራዊ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ለማጎልበትና እና የብሔራዊ መግባባት ተግባራትን ለማጠናከር ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ያስመሰከረ ሲሆን ወጣቶች እድል ከተሰጣቸው ሀገራቸውን ለማገልገል እና ወደ እድገት ለመምራት ወሳኝ የማህበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!