በጋምቤላ ክልል የሰላም ኮንፍረንስ ተካሄደ
Asset-Herausgeber
ታህሳስ 23 ቀን 2017ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፤ የሰላም ሚኒስቴር ከጋምቤላ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩጌታ ገነነ በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህብረሰተቡ የሰላም ባለቤት በመሆን ሰላሙን ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ቸሩጌታ አክለውም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ደህንነቱ እንዲረጋገጥ ህብረተሰቡ ቀዳሚ የሰላም ባለቤት በመሆን ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲያጠናክርም አደራ ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና የብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለምቶ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲውል ተቋሙ በዋናነት በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ።
በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ በዘላቂነት እንዲቀጥል ማድረግ ሁላችንም በአንድነት ጽኑ አቋም ይዘን በሰላም ግንባታ ዙሪያ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅብንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኮንፍረንሱ የጋምቤላ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ሰላም ለአንድ ሀገር ህዝብ ህልውና መሰረት ነው ያሉ ሲሆን ሰላም ከሌለ ልማት፣እድገት፣ወጥቶ መግባት አይቻልም። ስለሆነም በጋምቤላ ክልል የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማፅናት የአብሮነት እሴቶቻችንን እናጠናክራለን ብለዋል።
ሰላም ደክመን፣ብዙ ጥረት አድርገን የምናመጣው ሳይሆን አብሮን የተፈጠረ ፣በእጃችን የሚገኝ ነገርግን ካልተጠቀምንበት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን የተፈጥሮ ስጦታ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ ብቸኛ ምርጫችን የሆነውን ሰላም ለማደፍረስ ህዝብን ሽፋን በማድረግ የግል አላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማውገዝ ለዘመናት አብሮን የኖረውን ወንድማማችነት ፣መቻቻል ፣መደጋገፍ ፣አብሮነትን በማጠናከር በክልላችን የተጀመውን የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል ይኖርብናልም ተብለዋል ።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሲደረግ በቆየውና እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ያልተቋረጠ ድጋፍና እገዛ ላደረገው ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሰላም ሚኒስቴርም ምስጋና አቅርበዋል ።
በመድረኩ ብዝሀነት፣መቻቻልና እርቀ ሰላም ለሀገራዊ አንድነትና ግንባታ የሚል ጹሁፍ የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ መምህር በሆኑት በአቶ ዘላለም በፍቃዱ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል ።