ሀገር ግንባታ
ሀገር ግንባታ
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት መንግስት መስርታና ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ናት ፡፡ በእነዚህ የታሪክ ዘመናት በነበሩት የመንግስታት ስርዓቶች ውስጥ በመልካምነት የሚጠቀሱ፣ ብዙ የትስስር ሰበዞች የተፈጠረባት፣ቀደምት ስልጣኔ ከነበራቸው አገራት መካከል የነበረች፣ በርከት ያሉ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ትሩፋቶች ያሉባት ሀገር ናት፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በጦርነት፣ በድህነትና በፖለቲካ ጥያቄዎች ተወጥራ የኖረች አሁንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለች ሀገር ናት፡፡
ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቷን ያስተዳደሯት መሪዎች ባመቻቸው መንገድ ሀገሪቷን ለመገንባት የሄዱበት መንገድ አገር ግንባታ /Nation Building/ ጉዞው ከሀገረ መንግስቱ ግንባታ/ State Building ጉዞ አንጻር ወደ ኃላ የቀረ በመሆኑ ነው፡፡
የአገር ግንባታ (Nation Building) ''የአንድ ማህበረሰብ ወይም ህዝብ አባላት የሚታወቁበት የጋራ መገለጫዎች” ፣የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ምልክት፣ ቅርስ ወይም ትውስታ የሚንፀባረቅበት “እንደ ህዝብ እኛ ማን ነን?” የምለዉን ጥያቄ የሚመለስበት የጋራ ምስል፣ የጋራ ስሜትና የጋራ አረዳድ ላይ ይመሰረታል። እንደ አንድ ህዝብ አባልነት ሰዎች ራሳቸዉን የሚመለከቱበት መነፅርም ነው።
የሰላም ግንባታ ሥራ ከአገር ግንባታ ጋር የጠበቀ ትስስር አለው ።የዜጎች የጋራ ሀገራዊ ማንነት ሲያድግ እና ሲጠነክር ሀገራዊ ስሜት እና አንድነታችን ያድጋል፣አንድነታችን ደግሞ የሰላማችን ዋስትና ነው። የሰላም ሚኒስቴር ለሀገረ ግንባታ ስራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ፤ የአገር ግንባታ ስራ የሁሉን ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ትውልድ የመገንባት ተግባር ነው ብሎም ያምናል።
የሀገር ግንባታ ስራ ስንል የምንፈልጋትን እና ሁላችንም የምንመኛትን ኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ ሲሆን፤ ሁላችንም የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በብልፅግና ከፍታ ያለችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገር ማየት ነው። የሀገር ግንባታ ስራ በሶስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል እነዚህም ሀገራዊ ማንነቶቻችን/የጋራ ማንነት/፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን እና ብሔራዊ እሴቶቻችን ናቸው።
ሰላም ለኢትዮጵያ!