"ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት ተካሄደ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ጳጉሜ 2/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) "ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ የኅብር ቀን አከባበርን በማስመልከት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና ልህቃን በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ሐመድ እድሪስ በፓናል ውይይት መክፈቻ ባሰሙት ንግግር ጥንታዊና ገናና ታሪክ ያላት ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅሙ የታሪክ ሂደት ውስጥ የገነባቻቸውን ገንቢ እሴቶች በመጠበቅ የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የመልክዓ ምድር ልዩነቶች ሳይገድቧቸው አንድነታቸውን አጠናክረው በየዘመናቱ ከውስጥና ከውጭ የተፈጠሩ ችግሮችን በመቋቋም የተለያዩ ድሎችን መጎናፀፋቸውን ገልፀዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ብዝኃነት አብሮነትን የሚያጠናክር መልካም ዕድልና ፀጋ ከመሆኑም ባሻገር በመተማመን ለመኖር የሚያስችል ጥበብ፣ ዕውቀት፣ የአንድነትና የአሸናፊነት ኃይል እንደሆነም አስገንዝበዋል።

“በአንድነት የጋራ ድሎቻችንን እና እሴቶቻችንን በማጎልበት የጋራ ትርክት ላይ በማተኮር ታላቅ የነበረችን ሀገር ወደ ገናናነትዋ እንድትደርስ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል” ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የጋራ አኩሪ ታሪክ፣ የጋራ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶቻችን፣ የጋራ ማህበራዊ እሴቶቻችንን፣ በደም የተሳሰረ፣ በኢትዮጵያዊነት የተጋመደ የጋራ ሀገራዊ ማንነት እና በጋራ የመበልፀግ ዕድላችንን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድል በማደስ ወደፊት መስፈንጠር ይኖርብናል ሲሉም መልእታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያሥላሴ በበኩላቸው ሀገራዊ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለመሻገር ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነን ካለፈው ታሪካችን ተምረን ለሀገራችን ሁለንተናዊ ለውጦች ስኬት ሀገራዊ ትርክትን ማስረጽ አንድነታችን እና አብሮነታችን እንዲጠናከር ፓናል ውይይቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

ብዝኃ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ መልክዓ ምድር፣ እንዲሁም ብዝኃ ዕውቀት መገለጫዋ የሆነው ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ሀብቶቻችን የአብሮነት ውጤት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ሲሆኑ “ኢትዮጵያዊያን አሁንም አዳዲስ ታሪኮችን በማስመዝገብ በትውልድ የሚዘከር ሥራ የመሥራት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን” ሲሉ በፓናል ውይይቱ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልእክት ተናግረዋል፡፡

ፓናል ውይይቱን የሰላም ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን “የጋራ ታሪካችን መገለጫዎቻችን”፣ “ማኅበራዊ ሀብቶቻችንና የአብሮነታችን ታሪካዊ መሠረቶች” እና “ሚዲያ ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገር ግንባታ ሊያበረክት የሚገባው ሚና” በሚሉ ርዕሶች ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡