"ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪና ማህበረሰብን ማቆራኘት ሲችሉ ኢትዮጵያ ታተርፋለች" - የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ
"ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪና ማህበረሰብን ማቆራኘት ሲችሉ ኢትዮጵያ ታተርፋለች" - የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር “ማህበራዊ ትስስራችን ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ቃል የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ሀገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ እያካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ ጠንካራ ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው አብሮነትና ትስስርን በማጉላት ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪና ማህበረሰብን ማቆራኘት ሲችሉ ኢትዮጵያ ታተርፋለች ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃልኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ያለባትን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ጠንካራ ትስስር ያለው ማህበረሰብ መፍጠር ከተቻለ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንድትችል እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማር የሚቀበሏቸውን ተማሪዎችን የቃል ኪዳን ቤተሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ጥልቅ ትስስር እንዲፈጥሩና ውጤታማ እንዲሆኑ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የመከበርና የትስስር ባህልን ተቋማዊ ቅርፅ እንዲይዝ ማድረጉን በመግለጽ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ የሚመጡ ተማሪዎችን አቅፎና ደግፎ ከማህበረሰቡ ጋር በማዋሀድ መደላድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
