ለሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
ለሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፤ የሰላም ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ለዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓት እና ግጭት አፈታት ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናው ለግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንተና ለመስጠት፣ የግጭትን ተለዋዋጭ ባህሪያትን ለመረዳት፣ የግጭት አውዶችን፣ መነሻዎችና እና መዋቅራዊ ምክንያቶችን ለመረዳት፣ የግጭት አፈታትና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ስትራቴጂ ለመቅረጽ የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር እና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓቱን ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ለማድረስ የተጀመሩ ሥራዎችንም የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በየደረጃው ያሉ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሮች ተቀናጅተው ከኅብረተሰቡ ጋር በትብብር በመሥራት በክልሉ ያለው ሰላም ተጠብቆ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስና ለሌሎች ግጭት ለሚታይባቸው አካባቢዎች ልምድ በሚወሰድበት ደረጃ ለማድረስ በስልጠና የአመራሮችን እና ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የስልጠናው አስተባባሪዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓት ላይ ለባለድርሻ አካላት የሚሰጡ ስልጠናዎች የዘርፉ አስፈጻሚዎች፣ ፈፃሚዎች እና ኅብረተሰቡ ተቀናጅተው እንዲሠሩ ስለሚያደርግ፤ ግጭት አመላካች እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል እና ቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳቸው ተመላክቷል፡፡
የሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ ም/ቢሮ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዓለማየሁ አሰፋ የሰላም ሚኒስቴር ለክልሉ እያደረገ ስላለው ድጋፍ እና ትብብር ምስጋና አቅርበው ስልጠናውን የወሰዱ አመራሮችና ባለሙያዎች ያገኙትን ግንዛቤ ካላቸው ልምድና ዕውቀት ጋር አዋህደው በመተግበር ውጤታማ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል፡፡