የሰላም ሚኒስቴር በዘላቂ ሰላም ግንባታ የግሉ ዘርፍ ሚናን በሚመለከት የውይይት መድረክ አካሂዷል
Asset Publisher
ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት እና ከሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ (CIPE) ጋር በመተባበር በዘላቂ ሰላም ግንባታ የግሉ ዘርፍ ሚናን በሚመለከት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ ንግድ በማኅበረሰባችን ጠንካራ ግንኙነት የሚፈጥርና አብሮነትን የሚያጠብቅ ገመድ መሆኑን በማስገንዘብ፤ በህብረተሰባችን ውስጥ ዘላቂ ግንኙነት እንዲኖር ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም "ሰላም ለንግዱ ማህበረሰብ የደም ስር ነው" ያሉ ሲሆን ሰላም ከሌለ ፋብሪካዎች ከስራ ይወጣሉ፣ ንግድ ይስተጓጎላል፣ ሰራተኛው ወጥቶ መግባት ይቸገራሉ ስለሆነም ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም ሰላም የሁላችንም ድምር ውጤት በመሆኑ የግሉ ዘርፍም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ግንባታ የአንበሳ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ የንግዱ ማህበረሰብ ለአብሮነት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው ሰላምን ለማስፈንና ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ከሌሎች ወገኖች የሚጠበቁ ኃላፊነቶች የመኖራቸውን ያህል ከግሉም ዘርፍ የሚጠበቁ በርካታ ኃላፊነቶች በመኖራቸው ድርሻውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ "የጋራ ትርክት ግንባታ እና ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ የግሉ ዘርፍ ሚና" የሚል ጹሁፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር በክቡር ሙዋዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቀረበ ሲሆን "በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ የግሉ ዘርፍ ሚና" የሚል ጹሁፍ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ በክቡር ቀነኒሳ ለሚ(ዶ/ር) ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡