
ሰላም የሚሰፍነው፤ግለሰባዊ እና ማህበራዊ ደህንነት ሲረጋገጥ፣ ፍትሃዊ የሕዝቦች ተጠቃሚነት ሲሰፍን፣ የሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ ሲኖር፤ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ፣ የእርስ በእርስ ትስስር ሲጠናከር እና መረዳዳትና መተሳሰብ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ማለት ሰላም ከሰው ልጅ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ የባህሪ እና የኑሮ ዘይቤ እሴቶችና ባህል ጋር ይተሳሰራል፤ ከጤና ደህንነት ከአካባቢ እና ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሁም ደህንነት ጋር ይያያዛል፤ ከልማት እና ከዕድገት ጋር ይተሳሰራል፤ ከፖለቲካዊ ሥርዓት እና መረጋጋት ጋር ቁርኝት አለው፤ ከእኩልነት፣ ከፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ ከተረጋጋ መዋቅራዊ እና ሕጋዊ ሥርዓቶች መኖር ጋር ይተሳሰራል፤ የጋራ ታሪክ እና የወል ትርክት ግንባታም የሰላም መሰረቶች ናቸው።
ዘላቂነት ያለው ሰላም ለሀገር ልማት እና ዕድገት መሰረት በመሆኑ፤ ለንግድ ድርጅቶች በቀላሉለመሸጥ እና ለመለወጥ፣ ለሥራ ፈጣሪዎች እና ለሳይንቲስቶች አዳዲስ ነገሮችን እንዲፈጥሩ፣አርሶ አደሩ እንዲያመርት እና እንዲሸጥ፣ ማኅበረሰቡም ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ያለ ደህንነት ስጋት እንደልብ እንዲያከናውን፣ መንግሥታት ውጤታማ በሆነ መንገድ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ፣ እንዲያስተባብሩ እና አንዲመሩ የሚያስችል ፀጋ ነው። ሰላም!! እንኳን በሕይወት ላሉት ፍጥረታት በመቃብር ላሉት ለሙታንም እረፍት ሰላም ዋጋ አለው!!! ስለሆነም ሰላም በእጃችን ነው፡፡ ለሰላም እንስራ፣ ሰላምን ለማረጋገጥ እንትጋ፣ እንጽና!! የሰላም ባለቤት ሁላችንም ነን!!