ስለ እኛ
የሰላም ሚኒስቴር በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ተቋማዊ፣ ዘላቂ እና ውጤታማ ለማድረግ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 የተቋቋመ የሰላም ዘርፍን የሚመራ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ ተቋም ነው፡፡

ተልዕኮ
በመላ ሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባትን እንዲሁም አንድነትን በማስፈን የዜጎችን፣ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦችን ሰላም እና ደህንነት በመጠበቅ እና በማጎልበት፣ የፌዴራል ሥርዓቱ በማጠናከር፣ ግጭቶችን በንቃት በመከላከል እና በመቆጣጠር፣ ክልላዊ እንዲሁም አህጉራዊ ትብብርን በማሳደግ እና ዘላቂ የሰላም ተግባራትን ተቋማዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን።
ራዕይ
የዜግነት ክብር፣ ሰላም እና ህብረ-ብሄራዊ አንድነት ማጎልበት።
ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች
1.ከሰላም ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ሕጎችን ለማውጣት የሚያስችሉ ሀሳቦችን ያመነጫል፣ ሲጸድቁም በሥራ ላይ ያውላል፤
2.የሀገር ውስጥ ሰላምን ለማስጠበቅ አግባብ ካላቸው የፌደራልና የክልል መንግሥታት አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል፤ የሀገርና ሕዝብ ሠላም እንዲከበር የሚያስችል ስልት ይነድፋል፤ የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራዎችን ያከናውናል፤
3. በተለያዩ ሃይማኖቶችና እምነቶች ተከታዮች፣ እንዲሁም በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ሰላምና መከባበር እንዲሰፍን ለማድረግ አግባብ ካላቸው የመንግሥት አካላት፣ የባህልና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፤
4.በሃይማኖት፣ በብሔርና ሌሎች ምክንያቶች ሽፋን የሚደረግ የአክራሪነትና የጽንፈኛነትን አስተሳሰብ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን ይቀይሳል፣ ያስፈጽማል፤
5.በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አግባብነት ያላቸውን አካላት ያስተባብራል፤ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመንግሥት ያቀርባል፤ ሲወሰንም አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
6.ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጎለብት የባህል ልውውጥ፣ የሥነዜጋ ትምህርት የሚስፋፋበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
7.በሕብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና ንቅናቄ ስልቶችን ይቀይሳል፣ አተገባበሩን ይከታተላል፤
8.ለአካባቢያዊ ግጭቶች መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ይለያል፤ ኅብረተሰቡ ወደ ግጭትና አለመረጋጋት እንዳያመራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያመለክት ጥናት ያቀርባል፣ ሲወሰንም ተግባራዊ ያደርጋል፤
9.በፌደራል መንግሥትና በክልሎች መካከል በመግባባትና በአጋርነት ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር በማድረግ የፌደራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የግንኙነቱ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፤
10.በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ ፵፰ እና ፷፪ ንዑስ አንቀጽ (፮) እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች ያመቻቻል፤
11. አግባብነት ያላቸው ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከክልሎች ጥያቄ ሲቀርብ በክልሎች ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በዘላቂነት የሚፈቱበትን መፍትሔ ይቀይሳል፣ ተግባራዊ ያደርጋል፤
12.የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ሲወሰን አፈጻጸሙን ያስተባብራል፤;
13.የሃይማኖት ድርጅቶችን ይመዘግባል፤
እሴቶች
- ሀገር-ወዳድነት
- ሰላማዊነት
- ህጋዊነት
- ምክንያታዊነት
- ዓለም-አቀፋዊነት